No products in the cart.

Contacts

92 Bowery St., NY 10013

thepascal@mail.com

+1 800 123 456 789

Category: CHARITY

blogCHARITYUncategorizedVOLUNTARISM

መጻጉዕን በመቄዶንያ

መጻጉዕን በመቄዶንያ

Mental Health Fair at Mekedonia

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር “መጻጉዕን በመቄዶንያ” በሚል መርህ ሐሳብ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የስነ-አዕምሮ (Mental Health) የሕክምና አገልግሎት (Health Fair) ለመስጠት በዝግጅት ላይ ይገኛል። በዚህ አገልግሎት ለመሳተፍ የምትፈልጉ ከዚህ በታች የተዘረዘሩ ባለሙያዎች የምዝገባ ቅጹን በመሙላት አውንታችሁን እንድታሳውቁን በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን።

ቀን፡ መጋቢት 3-10 // Date: March 12-19
ቦታ፡ መቄዶንያ የአረጋውያንና አእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል

ለዚህ አገልግሎት የሚያስፈልጉ ባለሙያዎች የሚከተሉት ናቸው፦

Specialties needed are the following:

  1. Psychiatrists
  2. Psychiatric Residents
  3. Psychiatric Nurses
  4. Psychologists
  5. General Practitioners
  6. Social Workers
  7. Nurses
  8. Pharmacists

To register please click the link below:

https://docs.google.com/forms/d/e/1FAIpQLSecfzTdlqnR0JlENVHRozBUuQA_HCbXoZXVm1Fgb-Ir-q8-Bg/viewform?usp=pp_url

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር ለሁሉም በሁሉም!
EOTMA for all by all!

 

CHARITYVOLUNTARISM

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር ወደ ዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም ያደረገው የሕክምና ጉዞ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር ወደ ዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም ያደረገው የሕክምና ጉዞ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር ከተመሰረተበት ዓላማ አንዱ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎችና የህብረተሰባችን ክፍሎች የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን፤ እግዚአብሔር በአምሳሉ የፈጠረውን የሰው ልጅ በሙሉ ኃይማኖትን፣ ብሔርን፣ ጾታንና የኑሮደረጃን ሳይለይ ለሁሉም ሰብአዊ አገልግሎትን መስጠት ነው። ከዚህም በመነሳት በተለያዩ ጊዜያት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን ይህን ሰብአዊ አገልግሎት በመስጠት በተጓዳኝ ከሕክምና ርቀው ወደ ሚገኙ ገዳማት በመጓዝ የጤና አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን ስንሰራ ቆይተናል። አሁንም በልዑል እግዚአብሔር አጋዥነት ወደ ታላቁ ዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም የሕክምና ጉዞ አከናውነናል።
በዚህም የሕክምና ተልዕኮ ጉዞ፡-
♱ 40 ከተለያዩ ስፔሺያሊቲ የተውጣጡ ባለሙያዎች ሙያዊ አገልግሎት ሰጥተዋል
♱ የውስጥ ደዌ፣ የዐይን፣ የጥርስ፣ የአንገት በላይ፣ የቆዳ ሐኪሞች፣ ፋርማሲስቶችና ነርሶች ተሳትፈዋል
ከመንገዱ አስቸጋሪነት የተነሳ ተራራማውንና የመንገዱን የመጨረሻውን ምዕራፍ በጭነት መኪና በመጓዝ ወደ ገዳሙም እንደደረስን ገዳማውያኑ በፍጹም ትህትና እና አክብሮት ተቀበሉን። ተንበርክከውም በቅዱሳን እጆቻቸው እግሮቻችንን አጠቡን። የፍቅር ማዕድም አቀረቡልን።
♱ በአገልግሎቱም 229 ታካሚዎች ተጠቃሚ ሆነዋል
✞ ገዳማውያን፣ የአብነት ት/ቤት መምህራንና ተማሪዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል
♱ 87 ታካሚዎች የዐይን ሕምና አግኝተዋል
✞ 79 የማንበቢያ መነጽሮች ተሰጥተዋል
✞ 18 ታካሚዎች የጥርስ ሕክምና ያገኙ ሲሆን፤ 11 ታካሚዎች የጥርስ ነቀላ ተሰርቶላቸዋል
ባህታዊ ፍስሀ በላቸው ከ40 ዓመት በላይ በገዳሙ ያገለገሉ አባት ሲሆኑ የጤና ባለሙያው ወደ ገዳማት የሚያደርገውን የሕክምና አገልግሎት ጉዞ ሲገልጹ “ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ለማዳን ወደዚች ምድር እንደመጣ ሁሉ እናንተም እኛን ለማገልገል ወደዚህ መጣችሁ” በማለት በአባታዊ አንደበታቸው ተናግረዋል።
ስለ ጽድቅ ብለው ዳዋ ጥሰው፤ ጤዛ ለብሰው፤ ድንጋይ ተንተርሰው፤ ማቅ ለብሰው፤ ግርማ ሌሊትን፣ ፀብአጋንንትን፣ ድምፀ አራዊትን፣ ረሐቡንና ጥሙን ችለው፤ ዓለምን ንቀው ፤ከሰው ርቀው፤ በጾምና በጸሎት ተወስነው የሚኖሩትን አባቶችና እናቶች ማገልገል ምንኛ መታደል ነው?
የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም ጸሐፊ አባ ኪዳነማርያም ጥላሁን በአገልግሎቱ መደሰታቸውን በመግለጽ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል እንዲሁም ወደ ሌሎችም ገዳማት አገልግሎቱን ተደራሽ እንዲያደርግ ከአባታዊ አደራ ጋር ገልጸዋል።
የሕክምና አገልግሎታችንን በማጠናቀቅ ታላቅ መንፈሳዊ በረከትን ተቀብለን ወደ ዝቋላ ተራራ በወጣንበት የጭነት መኪና የመልስ ጉዟችንን ጀመርን። የገዳማውያኑ ትህትና፣ አክብሮትና ፍቅር በህሊናችን እየተመላለሰ ቅዱስ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው” ያለውን ቅዱስ ቃል እያሰብን ቁልቁለቱን ወረድን። ከዚህ በመቀጠል ተመሳሳይ የህክምና አገልግሎት የምንሰጥበትን ቅዱስ ቦታ እያሰብን ልቦናችንን ለመጪው የበረከት ሥራ አዘጋጅተን የተሳካ ጉዟችንን አጠናቀቅን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር
ለሁሉም በሁሉም!
አባልም ይሁኑ!በአባልነት ለመመዝገብ ይህን ሊንክ ይጠቀሙ:
www.eotma.org/join

 

CHARITYVOLUNTARISM

ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉና በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖቻችን የሕክምና ጉዞ በደብረብርሐን ከተማ

ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉና በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖቻችን የሕክምና ጉዞ በደብረብርሐን ከተማ

ህዳር 26/2014 ዓ.ም

ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉና በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖቻችን  የሕክምና ጉዞ በደብረብርሐን ከተማ ተካሄደ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር ህዳር 26/2014 ዓ.ም ከተለያዩ የጤና ሙያ የተውጣጡ 25 ባለሙያዎችን ያካተት ቡድን በመያዝ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቀለው በደብረብርሐን መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችንና በጦርነቱ ተጎድተው በደብረብርሐን ሆስፒታል ለሚገኙ ቁስለኞች በቦታው በመገኘት የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ችሏል።

በዚህ አገልግሎት የተሳተፉ የባለሙያዎች ስብጥር እንደሚከተለው ነው፡

• የዉስጥ ደዌ ስፔሺያሊስት

• የማህጸን ስፔሺያሊስት

• የህጻናት ስፔሺያሊስት

• የጥርስ ስፔሺያሊስት

• የፊይዚዮ ቴራፒስት ባለሙያዎች

• የፕላስቲክ ቀዶጥገና ስፔሺያሊስት

• የስነ አእምሮ ባለሙያዎች

• ነርሶች

• ፋርማሲስቶችና ሌሎችም ባለሙያዎች የተሳተፉበት

የተከናወኑ ስራዎች፤

1. ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ:¬

• በ2 መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች በተለይም ነፍሰጡርና የሚያጠቡ እናቶች፣ ህጻናትና አረጋዊያን ሙሉ ህክምና ከተሟል መድኃኒት ጋር ተሰጥቷል

• በተለያዩ የስነ አእምሮ ህመሞች ለተጠቁት ወገኖቻችን በባለሙያ ህክምና ተሰጥቷል • 30 ካርቶን አልባሳት ከስዊድንና እስካንዴኒቪያ ምዕመናን በብፁዕ አቡነ ኤሊያስ አስተባባሪነት የተሰበሰበ ለተፈናቃዮች ታድሏል

2. በጦርነቱ ለተጎዱ ቁስለኞች

• በደብረብርሐን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ውስጥ ለሚገኙ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን የተሰጡ የህክምና አገልግሎቶች

♱ በ 3 ዋርድ ውስጥ የሚገኙ ከ 80 በላይ ቁስለኞች ታይተዋል

♱ የአጥንት፣ ጡንቻና ነርቭ ጉዳት የደረሰባቸውን የመመርመር እና የሚያስፈልጋቸውን ሕክምና የመለየት ስራ ተካሂዷል

♱ ስፕሊንት (Splint) የሚያስፈልጋቸውን በመለየት ተደርጎላቸዋል

♱ ፊዚዮቴራፒ በመስጠት መንቀሳቀስ ለተቸገሩ ወገኖች የተሻለ አካላዊ ጥንካሬና እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው አግዘናል

♱ የቁስል ህክምና (wound care) ተሰጥቷል ♱ የህመም ማስታገሻ (pain management) ህክምና ተሰጥቷል

♱ በደብረብርሐን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ለሚገኙ ባለሙያዎች የስፕሊንት አጠቃቀምና የፊዚዮቴራፒ ስልጠና በመስጠት ህክምናውን በቀጣይነት እዛው በሚገኙ ባለሙያዎች መስጠት የሚያስችል ስራ ተሰርቷል

♱ ከፍተኛ የአጥንትና ፕላስቲክ ቀዶ ጥገና (Orthopedics and plastic surgery) የሚያስፈልጋቸው ተለይተው ወደ አዲስ አበባ እንዲላኩ ተደርጓል

3. የመድሐኒት እርዳታ፡

• ማኅበሩ እጥረት ያጋጠሙ መድሐኒቶችን የሰሜን ሸዋ ዞን የጤና ቢሮ ኃላፊዎች በተገኙበት ርክክብ አድርጓል

4. በቀጣይ ሊደረጉ የሚገባቸው ስራዎች

• የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር ከዚህ ቀደም በደሴ አሁንም በደብረብርሐን ያደረገው የሕክምና አገልግሎት የችግሩን ግዝፈት በመረዳት ትኩረት የሚሻቸውን ተግባራት ለመለየት ችሏል። በዚህ ላይ ያተኮረ ቀጣይነት ያለው አገልግሎት ችግሩ በተከሰተባቸው በየትኛውም የአገራችን ከፍል ወደሚገኙ ወገኖቻችን ተመሳስይ ጉዞ የምናደርግ ይሆናል። ለዚህም የሁላችንን እገዛ ይጠይቃል። የአገልግሎታችን ተደራሽነት እንዲጨምር የበኩሎን እርዳታ ይለግሱ።

 ኢ.ኦ.ተ.ሕ.ማ ለሁሉም በሁሉም!

#eotma

#eotma_for_all_by_all

#ኢኦተሕማ_ለሁሉም_በሁሉም

 

CHARITYVOLUNTARISM

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን በደሴ ያደረገው አገልግሎት

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን በደሴ ያደረገው አገልግሎት

መስከረም 11-16/2014 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በደሴ ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችንን በቅርብ ካሉ የጤና ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ከመስከረም 11-16/2014 ዓ.ም ለ 6 ቀናት የቆየ ነጻ የሕክምና አገልግሎት በተሳካ ሁኔታ አከናውኗል።
ይህ ነጻ የሕክምና አገልግሎት የተሰጠባቸው 7 ጊዜያዊ መጠለያዎች የሚከተሉት ናቸው፤
1. አዲስ ፋና ት/ቤት
2. ካራጉቱ ት/ቤት
3. ትግልፍሬ ት/ቤት
4. አዲስአለም ት/ቤት
5. ንጉስ ሚካኤል(1ኛ ና2ኛደረጃ) ት/ቤት
6. ልጅ ኢያሱ ት/ቤት
7. ቅዳሜ ገበያ ት/ቤት
በጠቅላላው 760 ታካሚዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሲሆኑ ከዚህም ውስጥ 120 ህጻናት ይገኙበታል።በዚህም ወቅት አጅግ አጣዳፊ የሆነ የጤና ችግር የተገኘባቸው 20 ታካሚዎች ለከፍተኛ ህምና ወደ ሆስፒታል በሪፈራል ተልከዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር በዚህ ነጻ የሕክምና አገልግሎት የመድኃኒት አቅርቦትና ሌሎች ወጭዎችን በመሸፈን የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል።
በዚህ ሰብዓዊ የሕክምና አገልግሎት ላይ የተሳተፋችሁ የጤና ባለሙያዎች በሙሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር በእግዚአብሔር ስም ከፍ ያለ ምስጋና ያቀርባል።

CHARITYVOLUNTARISM

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር የመጀመሪያ የሕክምና ተልዕኮ ጉዞ ወደ ደብረሊባኖስ ገዳም

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር  የመጀመሪያ የሕክምና ተልዕኮ ጉዞ ወደ ደብረሊባኖስ ገዳም

መስከረም 9 ቀን 2014 ዓ.ም

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር ያዘጋጀውን የመጀመሪያ የህክምና ተልዕኮ ወደ ደብረሊባኖስ ገዳም እጅግ በተሳካ ሁኔታ መስከረም 9 ቀን 2014 ዓ.ም ላይ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ አከናውኗል። በዚህ የህክምና ጉዞ፡

♱ ከ 25 በላይ ከተለያዩ የህክምና ሙያ የተውጣጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል

♱ የዓይን፣ የጥርስና የውስጥ ደዌ ህክምና ተሰጥቷል

♱ ከ 200 በላይ የሚሆኑ ካህናት አገልጋዮች፣ መነኮሳት፣ የአብነት ትምህርት ቤት መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል

♱ 80 የንባብ መነጽሮች ታድለዋል

♱ ከ1100 በላይ የተለያዩ መድሐኒቶች ተሰጥተዋል

ለዚህም የተሳካ አገልግሎት በፀሎት፣ በቁሳቁስና በገንዘብ ላገዛችሁን በሙሉ የጻድቁ አቡነ ተክለኃይማኖት አማላጅነትና በረከት በሁላችን ላይ ይደር። ለቀጣዩ ተመሳሳይ የህክምና ተልዕኮ በድረ ገጻችን www.eotma.org በመሔድ በልገሳ (donation) እንዲሳተፉ እንዲሁም የማኅበሩ ዓባል በመሆን በበረከት ሥራ እንዲሳተፉ ከወዲሁ በእግዚአብሔር ስም እንጋብዛለን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር።

CHARITYVOLUNTARISM

የሕክምና ተልዕኮ ጉዞ ወደ ታላቁ ምሁር ኢየሱስ ገዳም የካቲት 5/2014 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር 7ኛው የሕክምና ተልዕኮ ጉዞ ወደ ታላቁ ምሁር ኢየሱስ ገዳም

የካቲት 5/2014 ዓ.ም

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር 7ኛውን የሕክምና ተልዕኮ ጉዞ ወደ ታላቁ ምሁር ኢየሱስ ገዳም በየካቲት 5/2014 ዓ.ም አደረገ። የሕክምና ቡድኑ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ጉራጌ ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና ሲደርስ የአዲስ አበባና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጸዴቅ ተቀብለዋቸዋል። በጉራጌ ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና በመገኘት የብፁዕነታቸውን ቡራኬ ተቀብለው በብፁዕ አባታችን የተባረከውን ጸበል ጸዲቅ ከቀመሱ በኋላ ጉዟቸውን ወደ ታላቁ ምሁር ኢየሱስ ገዳም አቀኑ።

ወደ ገዳሙ እንደደረሱም የገዳሙ አባቶችና የአብነት ተማሪዎች እጅግ በሚደንቅ ፍቅርና አክብሮት ተቀብለዋቸዋል። በጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌነት የሚኖሩት ገዳማውያን በፍጹም ትህትና እግራቸውን ተንበርክከው አጠቧቸው።  የፍቅር ማዕድም አቀረቡላቸው። የምሁር ኢየሱስ ገዳም አበምኔት አባ ዘኢየሱስ ወጋየሁ በጸሎት ባርከው ያዘጋጁላቸውን ማዕድ ተመግበው የሕክምና አገልግሎታቸውን በታላቅ መንፈሳዊ ደስታና እርካታ ማከናወን ጀመሩ።

በዚህ የሕክምና አገልግሎት 42 ከተለያዩ ስፔሺያሊቲ የተውጣጡ ባለሙያዎች ሙያዊ አገልግሎት ሰጥተዋል። የውስጥ ደዌ፣ የልብ፣ የዐይን፣ የጥርስ፣ የአንገት በላይ፣ የቆዳ፣ የስነ-አዕምሮ፣ የሕብረተሰብ ጤና፣ ፋርማሲስት እና ሌሎችም ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

በአገልግሎቱም 170 ታካሚዎች ተጠቃሚ ሆነዋል። ከነዚህም ውስጥ ገዳማውያን፣ የአብነት ት/ቤት መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ይገኙበታል።

የአገልግሎቱ አይነት

የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ብዛት

የውስጥ ደዌ ሕክምና 91
የዐይን ሕምና

·       የዐይን መነጸር የተሰጣቸው

71

27

የጥርስ ሕክምና

·       የጥርስ ነቀላ (extraction) እና እጥበት (Dental cleaning & scaling)

29

16

የአንገት በላይ ሕክምና 17
የቆዳ ሕክምና 15
የስነ አዕምሮ ሕክምና 12
የልብ ሕክምና 7
የቀዶ ጥገና ሕክምና 1

ከዚህም በተጨማሪ ለሁሉም ታካሚዎች የተሟላ መድኃኒት በነጻ ለመስጠት ተችሏል።

የሕብረተሰብ ጤና ባለሙያዎችም የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ምልከታ አካሂደዋል፤ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችም ለገዳሙ ተለግሷል።

በአገልግሎቱም መደሰታቸውን በዕለቱ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የነበሩት ገዳማዊያን፣ የአብነት ት/ቤት መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የምሁር ኢየሱስ ገዳም አበምኔት አባ ዘኢየሱስ ወጋየሁ የተሰጠውን የሕክምና አገልግሎት ሲገልጹ  “በዓይነቱ አይተነው የማናውቀው ነገር ግን ሁልጊዜም የምንመኘውና ስንጸልይበት የነበረ”  አገልግሎት ነው በማለት በአገልግሎቱ ላይ የተሳተፉትን የጤና ባለሙያዎች አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር በዚህ ታላቅ አገልግሎት ላይ ለተሳተፉ የጤና ባለሙያዎችና የማኅበሩ አባላት በልዑል እግዚአብሔር ስም ምስጋና ያቀርባል።

ጥያቄ ካለዎት info@eotma.org ይላኩልን

የኢ.ኦ..ተ.ሕ.ማ. አባል ይሁኑ!

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር

ለሁሉም በሁሉም!

 

 

CHARITY

ወደ ወልድያ የተደረገ የሕክምና ጉዞ ጥር 21-23/ 2014 ዓ.ም

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር

ከ “እኔም ለሀገሬ በሀምፕተን ሮድስ ቨርጂኒያ” አባላት

በተደረገ የገንዘብ ድጋፍ 6ኛውን የሕክምና ጉዞ ወደ ወልድያ

ጥር 21-23/ 2014 ዓ.ም

በዚህ አገልግሎት ከተለያዩ የጤና ሙያ የተውጣጡ 48 ባለሙያዎች ተሳትፈዋል። ጠቅላላ ሐኪሞች፣ የውስጥ ደዌ፣ የልብ፣ የህጻናት፣ የዐይን እና የስነ-አዕምሮ ስፔሻሊስቶች፣ ነርሶች፣ ፋርማሲስቶች፣ ላቦራቶሪ ቴክኒሻኖች እና ሌሎችም ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
በጠቅላላው ለ 1,644 ታካሚዎች አገልግሎት ለመስጠት ተችሏል።
➊ የውስጥ ደዌ ሕክምና ያገኙ፡ 813
➤ የልብ ሕክምና፡ ከ 50 በላይ
➤ የልብ አልትራሳውንድ (Echocardiogram) የተሰራላቸው፡ 47
➤ የልብ ሰርጀሪ የሚያስፈልጋቸው፡ 4 ታካሚዎች ተለይተዋል
➤ ለከፍተኛ ህክምና በሪፈራል የተላኩ እና በሆስፒታሉ በመተኛት ሕክምናቸውን እንዲቀጥሉ የተደረጉ፡ 5
➋ የህጻናት ሕክምና ያገኙ፡ 259
➌ የዐይን ሕክምና ያገኙ፡ 347
➤ የተለያዩ የዐይን ሕክምና መስጫ መሳሪያዎችንና መድኃኒቶችን ለሆስፒታሉ የዐይን ክፍል ለግሰናል
➍ የስነ-አዕምሮ ሕክምና ያገኙ፡ 156
➤ በሆስፒታሉ የስነ-አዕምሮ ክፍል በመተኛት ሕክምናቸውን እንዲቀጥሉ የተደረጉ፡ 2 ታካሚዎች
➎ የተሟላ የላቦራቶሪ ምርመራ ተካሂዷል
➏ አስፈላጊ መድኃኒቶች ለሁሉም በነጻ ታድሏል
➐ 2,400 ካርቶን አልሚ ምግብ በምግብ እጥረት ለተጠቁና ተጋላጭ ለሆኑ ህጻናትና እናቶች አድለናል።
ለዚህ የሕክምና ጉዞ መሳካት በገንዘብ ላገዙን “እኔም ለሀገሬ በሀምፕተን ሮድስ ቨርጂኒያ” አባላት በአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ስም ምስጋና እናቀርባለን። የወልድያ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ላደረጋችሁልን ትብብር እናመሰግናለን። በዚህ አገልግሎት ላይ የተሳተፋችሁ የጤና ባለሙያዎችና የኢ.ኦ.ተ.ሕ.ማ. አባላት በሙሉ በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን።
ኢ.ኦ.ተ.ሕ.ማ. የሁሉም በሁሉም !
EOTMA for all by all !
CHARITY

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር በአፋር ያደረገው የሕክምና ጉዞ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

በአፋር ራዊ ክልላዊ መንግስት በዱፍቲ ሆስፒታልና በጭፍራ የመጠለያ ጣቢያ

እኔም ለሀገሬ በሃምፕተን ሮድስ ቨርጂኒያ የኢትዮጵያውያን መረዳጃ ማህበር በተገኘ ድጋፍ

የተደረገ ክምና ተልዕኮና ጉዞ

ታህሳስ 2325 2014 .

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር ዓላማ አድርጎ ከተነሳበት ግቦቹ መካከል የሕክምና እርዳታ ለሚያስፈልገው ወገናችን በፍፁም ክርስቲያናዊ ስነ- ምግባርና ሰብአዊ ስሜት አገልግሎቱን ማድረስ ከጀመረ ውሎ አድሯል። በፈጣሪያችን መልካም ፈቃድ በታታሪ የማህበሩ አባላት ሁለገብ እገዛና ተሳትፎ ከታህሳስ 23-25 2014 ዓ.ም ወደ አፋር ክልል ትልቅ የህክምና ተልዕኮ ይዞ ስለተጓዘው የህክምና ቡድን ጉዞ እና አጠቃላይ የህክምና የአገልግሎት አሰጣጥ ከዚህ በሚከተለው መንገድ ቀርቧል።

የሀገርን ዳር ድንበር ጠባቂ ፤ በተደጋጋሚም በአዋሽ ወንዝ መገንፈል እንዲሁም በሀገራችን ባለው ወቅታዊ እና አንገብጋቢ የሰላም እጦት ምክንያት ገፈት ቀማሽ ቢሆንም ወገኑን ያለ አንዳች መስፈርት መውደድን የሚያውቅበት ቆራጡን የአፋር ህዝብ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት በፈቃደኛ ልበ ቅን የማህበሩ አባላት የተዋቀረው የህክምና ቡድን ከንጋቱ 11፡30 ጀምሮ የጉዞ መነሻውን 5 ኪሎ መንበረ ፓትሪያክ ቅድስት ማርያም በር ላይ በማድረግ ነበር የተጀመረው። ጉዞውና ስራው ያማረ ይሆን ዘንድ‹‹ ሰላም እለኪን›› በማለት ከቅድስት ማርያም ቤተ-ክርስቲያን ደጀ ሰላም አገልግሎቱ ወደሚሰጥበት ቦታ የሚያደርሰን ተሽከርካሪ በመግባት የተልዕኮው መጀመሪያ ሆኗል።

ከዚህ በመቀጠል የማህበሩ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ዘላለም ይርጋ ሌሎች የተልዕኮው አባላት እህትና ወንድሞቻችን በዋና መስመራችን ላይ እየጠበቁን በመሆኑ ጉዞ መጀመር እንደሚኖርብን አሳስበዋል፡፡ ሹፌራችን ተሽከርካሪውን ፊቱን ወደ እንግሊዝ ኤምባሲ በማዞር በተለምዶ መገናኛ ወደምንለው ሰፈር ተጓዝን።  የአፋሩን የህክምና አገልግሎት እውን እንዲሆን ከወራት በፊት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በተደጋጋሚ በአካልና በስልክ በመነጋገር ለስኬት እንዲበቃ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጉ የነበሩት ዶ/ር ፍሰሀ ተክሌም ተገኝተዋል።

በዚህ አገልግሎት ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች ከተለያዩ የጤና ሙያ እና ስፔሺያሊቲ የተውጣጡ ሲሆን ቁጥራቸውም 33 ነበር። ሾፌራችን ሙቀት እንዳያስቸግረን የተሽከርካሪውን የአየር መቆጣጠሪያ አስተካክሎልን ፤  ልባችንን ቅዝቃዜ እንዳይሰማው ደግሞ መንፈሳዊ መዝሙር እያስደመጠን ጉዟችንን ቀጠልን።

እንደወትሮው ሁሉ በሁለት ሰይፍ የተሳሉት ሊቀጠበብት ዶ/ር ዘላለም ይርጋ ሁሉን ቻይ ጌታ ካመሰገኑ በኋላ “ጉዟችን የሰመረ እንዲሆን ተልኳችንንም በተገቢው መንገድ ፈጽመን መገኘት እንችል ዘንድ የፈጣሪን እርዳታ መጠየቅ ያስፈልገናል” ብለው በገለፁት መሰረት ለፈጣሪያችን ምስጋናችንን እና ተማፅኖታችንን አቅርበናል። ገና በጉዟችን መጀመሪያ በረባዳና ሞቃታማው የስምጥ ሸልቆ አካል በሆነው የአዲስ – አዳማ መንገድ ላይ እንገኛለን። በመንፈስ ግን በዚህ ጦርነት ቀዳሚ ገፈት ቀማሽ ከሆኑት ወገኖቻችን መካከል የህክምና ድጋፍን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ እገዛ ወደ ሚያስፈልገው እንኳን እርሱ ግመሉ ሳይቀር ለሀገሩና ለሰንደቁ ስላለው ክብርና እጅግ ድንቅ ጀብዱ የሚነገርለትን የአፋር ወገናችንን እንዴት ማገዝ እንደምንችል መብሰልሰል ይዘናል።

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሕክምና ማህበር ኃይማኖት፣ ብሔር፣ ዘር እና የመሳሰሉት አካባቢያዊ እና ሌሎች ተጽዕኖዎች ሳይገድበው ለሁሉም የሰው ልጅ ከሁሉም ሰብአዊ ፍጡር ጋር በመተባበር አገልግሎቱን ለማዳረስ ይተጋል። ይኽም በመሆኑ ዶ/ር ዘላለም እንዳስተዋውቁን ኢንስፔክተር ሀይደር መሀመድ የተባሉ ፤ የአፋር ክልል ተወላጅና የጤና ባለሙያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማህበር በአፋር ክልል ለተጎዱ ወገኖቻችን የሕክምና ድጋፍ ለማድረግ ማሰቡን በዶ/ር ፍሰሀ ተክሌ ከሰሙ ጀምሮ አብረውን ለመጓዝ ፍቃደኛ መሆናቸውን ገልፀው ይኸው ዛሬ በመካከላችን ተገኝተዋል።  ኢኒስፔክተር ሀይደር መሀመድ ማህበሩ “ለዚህ ትልቅ ዓላማ ስለጋበዘኝና በክልል ተፈናቅለው በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኞች የህክምና እርዳታ ለማድረግ መሆናችሁን በሰማው ጊዜ በተሰማኝ ጥልቅ ደስታ ምክንያት ቀኑ ረዝሞብኝ አልደርስ ብሎኝ ነበር “ሲሉ ቅንነት በተሞላው ሁኔታ ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ዘላለም ይርጋም የአፋሩ የሕክምና አገልግሎት በዱብቲ ሆስፒታልና በጭፍራ ለሚገኙ ተፈናቃዮች በሁለት ምድብ ለመስጠት እንደታሰበ ገለፃ ስጥተዋል። በመቀጠልም የውስጥ ደዌ ሕክምናን በተመለከተ አገልግሎቱን እንዴት ሊሰጥ እንደሚችል ዶ/ር ፍሰሀ ተክሌ አብራርተዋል። ዶ/ር ፍሰሀ ተክሌ gastroenterologist መሆናቸውን ለአዲስ የማህበሩ አባላት ራሳቸውን ካስተዋወቁ በኋላ የውስጥ ደዌ ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የታሰበው በጭፍራ ለሚገኙ ተፈናቃዮች መሆኑን በጥሩ ሁኔታ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡

በመቀጠልም በህጻናት ህክምና በኩል በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህጻናት ሀኪም የሆኑት ዶ/ር ሀና ሊሻን እዚህ የሕክምና ዘመቻ ላይ ለመሳተፍ እድሉን በማግኘቴ ላቅ ያለ ምስጋናዬን እያቀረብኩ በህጻናት ሕክምና በኩል የምጠብቃቸው Acute watery diarrhea, malnutrition, and pneumonia ይኖራሉ ብለን እንገምታለን በመሆኑም ህጻናትን በሕክምና ለማገዝ የሚያስፈልጉ ግብአቶች ለመያዝ ጥረት ማድረጋቸው ሊገልፁልን ችለዋል፡፡

ዱብቲ ሆስፒታል ውስጥ ለመስጠት ስለታሰበው የቀዶጥገና እና የፊዚዮቴራፒ ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የተዘጋጁት አባላት በምን መልኩ እንደተዘጋጁ ገለጻ ያደረጉት ዶ/ር ጌታው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፕላስቲክ እና ሪኮንስትራክቲቭ ሰርጅን መሆናቸውን ገልጸው በዱብቲ ሆስፒታል ለመስጠት ያሰብነው የቀዶጥገና ሕክምና ስብራት ያጋጠማቸውን እና tendon injury እንዲሁም skin graft የሚስፈልጋቸውን ወገኖቻችንን ለመርዳት ሙሉ OR ቡድን የተካተተ ሲሆን ለዚህም የሚስፈልጉትን ግብአቶች ይዘው ለመምጣት ጥረት ማድረጋቸውን ለማህበሩ አባላት አስረድተዋል፡፡

በመድኃኒት በኩል ምን አይነት ዝግጅት እንደተደረገ ገለፃ እንዲያደርጉ የተጋበዙት ወ/ሮ መዓዛ ተፈሪ እድሉን በማግኘታቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልፀው ፤ እንደተለመደው በእጃችን የሚገኘውን የመድኃኒት ዝርዝር በሙሉ ለሁሉም ዲፓርትመንቶች ለሚገኙ ሀኪሞች በመላክ ተገልጋዮች ይዘውት የሚመጡትን የመድኃኒት ማዘዣ (prescription) በማየት የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ማሰባቸውን አብራርተዋል።

በእናቶች ህክምና በኩል አገልግሎቱን በምን መልኩ ለመስጠት እንደታሰበ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጋበዙት ሲ/ር ገነት ሀብታሙ እራሳቸውን ሲያስተዋውቁ በነርሲንግ እያገለገሉ እንደሚገኙና ሁለተኛ ድግሪያቸውን በስነ- ምግብ (Nutrition) መያዛቸውን ለማህበሩ አዲስ አባላት ካስተዋወቁ በኋላ በ Gynecology and Obstetrics በኩል የሚድዋይፈሪ ባለሙያዎችም መኖራቸውንና የሚያስፈልጋቸውን ግብአቶች ይዘው መምጣታቸውን ገልፀዋል፡፡

በመቀጠል ከሀገረ አሜሪካ የመጡትን ሲ/ር ቤተልሔም ጌጡ ራሳቸውን እንዲህ በማለት አስተዋውቀዋል። “ሲ/ር ቤተልሔም የአይ. ሲ.ዩ ነርስ (ICU nurse) ባለሙያ ስሆን እስከዛሬ ድረስ ማህበሩ እያከናወነ ያለውን መልካም ተግባር በቅርብ እርቀት ላይ ሆኜ እየተከታተልኩና ከማኅበሩ የቦርድ አባላት ጋር ብዙ ጊዜ መወያየት የቻልኩ ሲሆን ዛሬ በአካል አፋር የሚገኙ ወገኖቻችንን ለመርዳት በሚደረገው ዘመቻ ላይ በአካል በመገኘቴ የተሰማኝን ላቅ ያለ ደስታ ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡ ማኅበሩን ከውጭ ሆነው በብዙ ነገር እየደገፉ ያሉትን ወንድምና እህቶች እንዲሁም በሀገር ውስጥ ያላችሁ ባለ ቅን ልብ የሕክምና ባሙያዎችን ለማመስገን እወዳለሁ፡፡ የዛሬውን ጉዟችን የሰመረ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ።” ሲሉ መልካም ምኞታቸውን አጋርተዋል።

ከዚህ በመቀጠልም የማኅበሩ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ዘላለም ይርጋ የአሁኑ የህክምና ጉዞ ከወትሮ በተለየ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ህጻናት አልሚ ማግብ መያዙንና አገልግሎቱንም ለመስጠት ሁለት ቀናት ማደር እንደሚስፈልግ ገልጸዋል። ለዚህ የህክምና ዘመቻ የሚያስፈልጉትን ወጪዎች እኔም ለሀገሬ በሃምፕተን ሮድስ ቨርጂኒያ የኢትዮጵያውያን መረዳጃ ማህበር በተገኘ ድጋፍ የሸፈነ በመሆኑ ከልብ በማኅበሩ አባላትና ድጋፍ በሚያስፈልገው የአፋር ህዝብ ስም አመስግነዋል፡፡

በመጨረሻም ዶ/ር ዘላለም ተጨማሪ ሀሳብ መስጠት ለሚፈልጉ አባላት እድል እንደሚሰጡ በገለጹት መሰረት ሲ/ር አማነሽ ትዕዛዙ የአይ ሲ ዩ ነርስ ባለሙያ እንደሆኑ ገልጸው ፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገኙ ተረጂዎችን ለመርዳት የአይሲዩ ባለሙያዎች በመካከላችን በመገኘታቸውና የተሳካ አገልግሎት አከናውነን እንደምንመለስ ያላቸውን እምነት አስተላልፈዋል፡፡

ሹፌራችን በዉይይት ላይ መሆናችንን ተገንዝበዉ አቋርጠዉት የነበረዉን መዝሙር በመክፈት ልባችንን መዝሙሩ ላይ አይናችንን የገጠሩ የህብረተሰብ ክፍል አኗኗር ላይ አድርገን እንዲሁም የኑሮ ሁኔታቸዉን በግርድፉ ከአዲስ አበባ ነዋሪ ጋር እያወዳደርን መተሐራ ላይ ከረፋዱ 4፡05 ደቂቃ ደረስን። እለቱም ቀዳሚ ሰንበት (ቅዳሜ) በመሆኑ ለቁርስ ወርደን ተመግበን ከጨረስን በኋላ 4፡45 ላይ መተሐራን ለቀን ጉዟችንን በመቀጠል ወደ ዱፍቲ ሆስፒታልና ጭፍራ መጠለያ ጣቢያ አቀናን።

በአዉራ ጎዳና ግራና ቀኝ ላይ የምናገኛቸዉ እጽዋት ‹‹የፀሀዩ ንዳድ ያጠቃት በብዙ ጠዉልጎ የሚታይ የቅጠሏ ወዙ………›› ብለዉ የገጠሙት ክብር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል በአፋር መንገድ ላይ ሆነዉ መሆን አለበት ያስብላል፡፡

የአምላክ ፈቃድ ሆኖ ፀሎታችንንም ሰምቶ ያለ አንዳች እንቅፋት 9፡30 ላይ በተዘጋጀልን ናዝሬት ሆቴል ቅጥር ግቢ ውስጥ ገባን።  የሆቴሉ አስተናጋጆች ብርሃን ፈገግታቸውን ሲያሳዩን ምንም እንኳን የመንገዱ ርቀት ያኽል ድካም ባይሰማንም ከአራት ሰዓት በላይ በመቀመጣችን ምክንያት የተፈጠረብንን የድካም ስሜት አባረው አንዳች መነቃቃት እንዲፈጠርብን ማድረግ ችለዋል፡፡ ተጨንቀውና ተጠበው ያዘጋጁልንን ምግብ በልተንና ጠጥተን ሆቴል ሳይሆን የዘመድ ድግስ ቤት የታደምን ያልመሰለው አንድም ሰው ማግኘት አይቻልም፡፡ ብሉልኝ ጠጡልኝ ተብለን የአፋርን ህዝብ እንግዳ ተቀባይነትና መልካምነት ገና በማለዳው ስራ ሳንጀምር ተረድተናል፡

ዶ/ር ዘላለም ይርጋ በሰላም ያደረሰንን አምላክ አመስግነው ለነገ ስራችን መቃናት የዱብቲ ሆስፒታልን መጎብኘት እና በተለይ ቀዶጥገና እና የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት የሚያስፈልጋቸውን ተረጂዎች ለመለየት ይረዳን ዘንድ ወደ ዱብቲ ሆስፒታል አቀናን። የሆስፒታሉን ኃላፊዎች በማግኘት ስለመጣንበት ዓላማ ገለጻ አደረግን። የሆስፒታሉም ኃላፊዎች መምጣታችን በእጅጉ እንደሚጠቅማቸው በአጽንዖት ገልጸውልናል። ከመካከላችን የኦ አር ቲም (OR team) ስራውን በቀጥታ መጀመር ያስፈልገውም ስለነበር እስከ ምሽቱ 1፡30 ድረስ በሆስፒታሉ ያሉትን የፕላስቲክ ሰርጀሪ ፣ፒኦፒ ፣ ካስት እና የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት (plastic, surgery, POP, and physiotherapy) የሚያስፈልጋቸውን የሆስፒታሉ ተረጂ ታካሚዎች በመለየት ለቀጣዩ ቀን እንዲዘጋጁ ከተደረገ በኋላ ለእራት ወደ ሆቴላችን ተመልሰናል። ጭፍራ ያሉትን ወገኞቻችንን ለመርዳት የግድ ከንጋቱ 11 ፡00 ሰዓት መነሳት እንዳለብን ተነጋግረን ለሆስፒታሉ አገልግሎት የሚሆኑትን መድኃኒቶችንና መሳሪያዎችን ኦ. አር ቲም (OR team) በሚገኝበት ሆቴል አሳደርን።

እንዲሁም ለተፈናቃዮች የሚሆኑትን መድኃኒቶች ከተለዩ በኋላ አምስቱ የማህበሩ አባላት እስከ ምሽቱ 5፡30 ድረስ የመጡትን መድኃኒቶች በቀጣዩ ቀን በየምድባቸው ለማድረግ በቂ ግዜ ስለማይኖረን በዕለቱ ማሰናዳት ስለነበረብን የመድሓኒቶችን ብዛትና አይነት ለይተን ለማስፈር ተሞክሯል፡፡ ይህንንም የመድኃኒት ዝርዝር ለባለሙያዎች በየግል ስልካቸው መላክ በመቻሉ ለስራው መቃናት በጎ አስተዋፅዖ ማበርከቱን ማወቅ ችለናል።

በቀጠሯችን መሰረት ከንጋቱ 11፡00 ላይ በጭፍራ የተፈናቃዮች ጣቢያ አገልግሎት ለመስጠት የተመደቡ አባሎችን ይዛ መኪናችን በሚሌ በኩል ወደ ጭፍራ ያመራን ሲሆን፤ የመልክዓ ምድሩ ሁኔታ ቀልባችንን እየገዛው ከአፋር ወደ ባቲ በሚወስደው አውራ መንገድ ላይ ከዋናው ከተማ 70 ኪሎ ሜትር ከተጓዝን በኋላ በቦታው ላይ የሚገኙትን ወገኖቻችንን ስንመለከት አንዳች ውስጥን የሚረብሽ እንግዳ ስሜት ተሰምቶን ነበር።

ኢንስፔክተር ሀይደር ከመኪናው በመውረድ የአፋርን ልጆች በቋንቋቸው በማውራቱ የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ የሚለው አባባል እውነታነቱ ከፍ ያለ እንደሆነ ተረድተናል። የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ከታካሚው ጋር መግባባት በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነው። ይህንንም ኢንስፔክተር እና በቦታው ላይ ያሉ የጤና ባለሙያዎች በቋንቋ ምክንያት ሊፈጠር የሚችለውን ክፍተት ስለቀረፉልን ቀልጣፋ አገልግሎት እንድንሰጥ ረድቶናል፡፡

ኢንስፔክተር ሀይደር በቦታው ላይ ያሉትን ኃላፊዎች ካነጋገረልን በኋላ መልካም ፈቃዳቸው ሆኖ በቀጥታ ቦታውን በማስተካከል ከጠዋቱ 3፡30 ጀምሮ አገልግሎት መስጠት ተጀምሯል።  በዋናነት አገልግሎቱ ያካትት የነበረው የውስጥ ደዌ፣ የህጻናት፣ የማህጸንና ጽንስ፣ የስነ አእምሮ እና የአይን ህክምናዎች ይገኙበታል፡፡

የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ካርድ ይሰጣቸውና ልየታ ላይ ቫይታል ሳይን (vital sign) ከተወሰደ በኋላ ወደሚመለከተው ክፍል በመሄድ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን ችለዋል፡፡ በተለያየ ምክንያት ከመጠለያ ድንኳናቸው ወጥተው ወደ ተዘጋጀው ስፍራ መምጣት የማይችሉ ይኖራሉ ተብሎ ስለታሰበ ሶስት ባለሙያዎች የቤት ለቤት ስራውን በተሳካ ሁኔታ ሊያከናውኑልን ችለዋል። እንደተለመደው የልየታውን ስራ በግንባር ቀደምትነት የምግባረ ሰናይ ሆስፒታል ሰራተኞች አከናውነውልናል፡፡ አገልግሎቱን በምንሰጥበት ወቅት የካርድ እጥረት ቢያጋጥመን እንኳን ወረቀቶችን በማዘጋጀት ስራችንን እስከ 7፡30 ድረስ ለመቀጠል ችለናል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የሚድዋይፈሪ እና የስነ አእምሮ ባለሙያዎች ቤት ለቤት ባደረጉት የሕክምና ድጋፍ ፖስት ትራውማቲክ እስትረስ ዲስ ኦርደር (post-traumatic stress disorder or PTSD) በከፍተኛ ሁኔታ እንዳጋጠማቸው መረዳት ተችሏል። ብዙዎች በ PTSD, depression እና ጭንቀት ተጠቂ ሲሆኑ ወጣቶችና ህጻናትም ከትምህርት ገበታቸው በመስተጓጎላቸው እንዲሁም ሞት፣ ጥፋትና ውድመትን በመመልከታቸው እና አንዳንዶቹም ከወላጆቻቸው በመለያየታቸው ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ይታይባቸው ነበር። የዘርፉ ባለሙያዎችም ያላቸውን ክህሎትና እውቀት ተጠቅመው በግልና በጋራ የምክር አገልግሎት ለመስጠት ተችሏል። በመጨረሻም ከአገልግሎት የተረፉንን መድኃኒቶች ለጤና ባለሙያዎች አስረክበናል።

በጭፍራ የመጠለያ ጣቢያ በተካሄደው የህክምና ዘመቻ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑ ተፈናቃዮች ብዛት: –

  1. በውስጥ ደዌ (Internal Medicine): 185
  2. በህጻናት (Pediatrics): 169
  3. በማህጸንና ፅንስ (Gynecology and Obstetrics): 62
  4. በዓይን (Ophthalmology): 41
  5. Nutrition: 960 ካርቶን አልሚ ምግብ በምግብ እጥረት ተጠቂ ለሆኑ ህጻናት፣ እናቶች እና 32 የ HIV ህሙማን ታድሏል።
  6. በስነ አእምሮ ሕክምና፡ 110 ታካሚዎች ሲረዱ፤ ከነዚህም ውስጥ
    1. 23-86 ዓመት እድሜ የሚገኙ 36 ሴቶች
    2. 7-11 ዓመት እድሜ የሚገኙ 48 ልጆች
    3. 14-18 ዓመት እድሜ የሚገኙ 26 ወጣቶች አገልግሎት ለመስጠት ተችሏል።

በጠቅላላው 527 ወገኖቻችን በጭፍራ የመጠለያ ጣቢያ አገልግሎት ማግኘት የቻሉ ሲሆን የተወሰኑት ከአንድ በላይ አከግሎት ተጠቃሚ ነበሩ። 6 ታካሚዎችም ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ዱፍቲ ሆስፒታል በሪፈራል ተልከዋል።

በዱብቲ ሆስፒታል ደግሞ በተካሄደው ህክምና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑ የታካሚዎች ብዛት

  1. ፕላስቲክ ሰርጀሪ (plastic surgery) ፡ 4
  2. ፊዚዮቴራፒና ካስት (Physiotherapy and applying cast with POP) 52

በድምሩ 56 ታካሚዎች በዱብቲ ሆስፒታል የቀዶጥገና፣ የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት እና የካስት ተጠቃሚ መሆን ችለዋልበአጠቃላይ በዱብቲ ሆስፒታልና በጭፍራ የመጠለያ ጣቢያ በተካሄደው የክምና ተልዕኮ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ብዛት 583 ናቸው፡፡

በመጨረሻም በሁለቱም ቦታዎች የነበሩት ባለሙያዎች ሀሳብና አስተያየት እንዲሰጡ ከተደረገ በኋላ ወደ መኝታችን በማምራት ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት ላይ ለአፋር ሕዝብ ሰላሙ እንዲመለስለት በመመኘት አፋርን ተሰናብተን ፤ ወደ አዲስ አበባ በሰላም ተመልሰናል፡፡

በአፋር ላደረግነው የሕክምና ተልዕኮና ጉዞ መሳካት የረዱንን በሙሉ ለማመስገን እንወዳለን በተለይም ይህን አገልግሎት በገንዘብ ለረዱን እኔም ለሀገሬ በሀምፕተን ሮድስ ቨርጂኒያ የኢትዮጵያውያን መረዳጃ ማኅበር  የላቀ ምስጋና እናቀርባለን። በመቀጠልም የአፋር ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰኢድ፣ የዱፍቲ ሆስፒታል ዳይሬክተር  መሐመድ የሱፍ፣ የአፋር ማገገሚያ ጣቢያ ኃላፊ ሼክ ኑሪ፣ የጭፍራ መጠለያ ጣቢያ ኃላፊ አቶ መሐመድ፣ አቶ ኢብራሒም አለሙ በሎጂስቲክስ አገልግሎት፣ ኢንስፔክተር ሀይደር የፌዴራል ፖሊስ ሆስፒታል ሰራተኛ፣ ናዝሬት ሆቴል በምግብ አቅርቦት፣ ቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል በመረጃ አቅርቦት፣ የአለርት ሆስፒታል ሙሉ የ OR team ከአስፈላጊ ግብዓቶች ጋር ስለ ረዱን እና በመጨረሻም በዚህ ተልዕኮ የተሳተፉ የማኅበራችን አባላትና የጤና ባለሙያዎች በሙሉ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ በሆኑ ወገኖቻችን እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር ስም ምስጋናችንን እናቀርባለን።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር ለሁሉም በሁሉም!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!

ጥር 1/2014 ዓ.ም