በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በዱፍቲ ሆስፒታልና በጭፍራ የመጠለያ ጣቢያ
“እኔም ለሀገሬ በሃምፕተን ሮድስ ቨርጂኒያ የኢትዮጵያውያን መረዳጃ ማህበር” በተገኘ ድጋፍ
የተደረገ የሕክምና ተልዕኮና ጉዞ
ታህሳስ 23–25 2014 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር ዓላማ አድርጎ ከተነሳበት ግቦቹ መካከል የሕክምና እርዳታ ለሚያስፈልገው ወገናችን በፍፁም ክርስቲያናዊ ስነ- ምግባርና ሰብአዊ ስሜት አገልግሎቱን ማድረስ ከጀመረ ውሎ አድሯል። በፈጣሪያችን መልካም ፈቃድ በታታሪ የማህበሩ አባላት ሁለገብ እገዛና ተሳትፎ ከታህሳስ 23-25 2014 ዓ.ም ወደ አፋር ክልል ትልቅ የህክምና ተልዕኮ ይዞ ስለተጓዘው የህክምና ቡድን ጉዞ እና አጠቃላይ የህክምና የአገልግሎት አሰጣጥ ከዚህ በሚከተለው መንገድ ቀርቧል።
የሀገርን ዳር ድንበር ጠባቂ ፤ በተደጋጋሚም በአዋሽ ወንዝ መገንፈል እንዲሁም በሀገራችን ባለው ወቅታዊ እና አንገብጋቢ የሰላም እጦት ምክንያት ገፈት ቀማሽ ቢሆንም ወገኑን ያለ አንዳች መስፈርት መውደድን የሚያውቅበት ቆራጡን የአፋር ህዝብ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት በፈቃደኛ ልበ ቅን የማህበሩ አባላት የተዋቀረው የህክምና ቡድን ከንጋቱ 11፡30 ጀምሮ የጉዞ መነሻውን 5 ኪሎ መንበረ ፓትሪያክ ቅድስት ማርያም በር ላይ በማድረግ ነበር የተጀመረው። ጉዞውና ስራው ያማረ ይሆን ዘንድ‹‹ ሰላም እለኪን›› በማለት ከቅድስት ማርያም ቤተ-ክርስቲያን ደጀ ሰላም አገልግሎቱ ወደሚሰጥበት ቦታ የሚያደርሰን ተሽከርካሪ በመግባት የተልዕኮው መጀመሪያ ሆኗል።
ከዚህ በመቀጠል የማህበሩ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ዘላለም ይርጋ ሌሎች የተልዕኮው አባላት እህትና ወንድሞቻችን በዋና መስመራችን ላይ እየጠበቁን በመሆኑ ጉዞ መጀመር እንደሚኖርብን አሳስበዋል፡፡ ሹፌራችን ተሽከርካሪውን ፊቱን ወደ እንግሊዝ ኤምባሲ በማዞር በተለምዶ መገናኛ ወደምንለው ሰፈር ተጓዝን። የአፋሩን የህክምና አገልግሎት እውን እንዲሆን ከወራት በፊት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በተደጋጋሚ በአካልና በስልክ በመነጋገር ለስኬት እንዲበቃ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጉ የነበሩት ዶ/ር ፍሰሀ ተክሌም ተገኝተዋል።
በዚህ አገልግሎት ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች ከተለያዩ የጤና ሙያ እና ስፔሺያሊቲ የተውጣጡ ሲሆን ቁጥራቸውም 33 ነበር። ሾፌራችን ሙቀት እንዳያስቸግረን የተሽከርካሪውን የአየር መቆጣጠሪያ አስተካክሎልን ፤ ልባችንን ቅዝቃዜ እንዳይሰማው ደግሞ መንፈሳዊ መዝሙር እያስደመጠን ጉዟችንን ቀጠልን።
እንደወትሮው ሁሉ በሁለት ሰይፍ የተሳሉት ሊቀጠበብት ዶ/ር ዘላለም ይርጋ ሁሉን ቻይ ጌታ ካመሰገኑ በኋላ “ጉዟችን የሰመረ እንዲሆን ተልኳችንንም በተገቢው መንገድ ፈጽመን መገኘት እንችል ዘንድ የፈጣሪን እርዳታ መጠየቅ ያስፈልገናል” ብለው በገለፁት መሰረት ለፈጣሪያችን ምስጋናችንን እና ተማፅኖታችንን አቅርበናል። ገና በጉዟችን መጀመሪያ በረባዳና ሞቃታማው የስምጥ ሸልቆ አካል በሆነው የአዲስ – አዳማ መንገድ ላይ እንገኛለን። በመንፈስ ግን በዚህ ጦርነት ቀዳሚ ገፈት ቀማሽ ከሆኑት ወገኖቻችን መካከል የህክምና ድጋፍን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ እገዛ ወደ ሚያስፈልገው እንኳን እርሱ ግመሉ ሳይቀር ለሀገሩና ለሰንደቁ ስላለው ክብርና እጅግ ድንቅ ጀብዱ የሚነገርለትን የአፋር ወገናችንን እንዴት ማገዝ እንደምንችል መብሰልሰል ይዘናል።
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሕክምና ማህበር ኃይማኖት፣ ብሔር፣ ዘር እና የመሳሰሉት አካባቢያዊ እና ሌሎች ተጽዕኖዎች ሳይገድበው ለሁሉም የሰው ልጅ ከሁሉም ሰብአዊ ፍጡር ጋር በመተባበር አገልግሎቱን ለማዳረስ ይተጋል። ይኽም በመሆኑ ዶ/ር ዘላለም እንዳስተዋውቁን ኢንስፔክተር ሀይደር መሀመድ የተባሉ ፤ የአፋር ክልል ተወላጅና የጤና ባለሙያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማህበር በአፋር ክልል ለተጎዱ ወገኖቻችን የሕክምና ድጋፍ ለማድረግ ማሰቡን በዶ/ር ፍሰሀ ተክሌ ከሰሙ ጀምሮ አብረውን ለመጓዝ ፍቃደኛ መሆናቸውን ገልፀው ይኸው ዛሬ በመካከላችን ተገኝተዋል። ኢኒስፔክተር ሀይደር መሀመድ ማህበሩ “ለዚህ ትልቅ ዓላማ ስለጋበዘኝና በክልል ተፈናቅለው በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኞች የህክምና እርዳታ ለማድረግ መሆናችሁን በሰማው ጊዜ በተሰማኝ ጥልቅ ደስታ ምክንያት ቀኑ ረዝሞብኝ አልደርስ ብሎኝ ነበር “ሲሉ ቅንነት በተሞላው ሁኔታ ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ዘላለም ይርጋም የአፋሩ የሕክምና አገልግሎት በዱብቲ ሆስፒታልና በጭፍራ ለሚገኙ ተፈናቃዮች በሁለት ምድብ ለመስጠት እንደታሰበ ገለፃ ስጥተዋል። በመቀጠልም የውስጥ ደዌ ሕክምናን በተመለከተ አገልግሎቱን እንዴት ሊሰጥ እንደሚችል ዶ/ር ፍሰሀ ተክሌ አብራርተዋል። ዶ/ር ፍሰሀ ተክሌ gastroenterologist መሆናቸውን ለአዲስ የማህበሩ አባላት ራሳቸውን ካስተዋወቁ በኋላ የውስጥ ደዌ ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የታሰበው በጭፍራ ለሚገኙ ተፈናቃዮች መሆኑን በጥሩ ሁኔታ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡
በመቀጠልም በህጻናት ህክምና በኩል በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህጻናት ሀኪም የሆኑት ዶ/ር ሀና ሊሻን እዚህ የሕክምና ዘመቻ ላይ ለመሳተፍ እድሉን በማግኘቴ ላቅ ያለ ምስጋናዬን እያቀረብኩ በህጻናት ሕክምና በኩል የምጠብቃቸው Acute watery diarrhea, malnutrition, and pneumonia ይኖራሉ ብለን እንገምታለን በመሆኑም ህጻናትን በሕክምና ለማገዝ የሚያስፈልጉ ግብአቶች ለመያዝ ጥረት ማድረጋቸው ሊገልፁልን ችለዋል፡፡
ዱብቲ ሆስፒታል ውስጥ ለመስጠት ስለታሰበው የቀዶጥገና እና የፊዚዮቴራፒ ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የተዘጋጁት አባላት በምን መልኩ እንደተዘጋጁ ገለጻ ያደረጉት ዶ/ር ጌታው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፕላስቲክ እና ሪኮንስትራክቲቭ ሰርጅን መሆናቸውን ገልጸው በዱብቲ ሆስፒታል ለመስጠት ያሰብነው የቀዶጥገና ሕክምና ስብራት ያጋጠማቸውን እና tendon injury እንዲሁም skin graft የሚስፈልጋቸውን ወገኖቻችንን ለመርዳት ሙሉ የ OR ቡድን የተካተተ ሲሆን ለዚህም የሚስፈልጉትን ግብአቶች ይዘው ለመምጣት ጥረት ማድረጋቸውን ለማህበሩ አባላት አስረድተዋል፡፡
በመድኃኒት በኩል ምን አይነት ዝግጅት እንደተደረገ ገለፃ እንዲያደርጉ የተጋበዙት ወ/ሮ መዓዛ ተፈሪ እድሉን በማግኘታቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልፀው ፤ እንደተለመደው በእጃችን የሚገኘውን የመድኃኒት ዝርዝር በሙሉ ለሁሉም ዲፓርትመንቶች ለሚገኙ ሀኪሞች በመላክ ተገልጋዮች ይዘውት የሚመጡትን የመድኃኒት ማዘዣ (prescription) በማየት የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ማሰባቸውን አብራርተዋል።
በእናቶች ህክምና በኩል አገልግሎቱን በምን መልኩ ለመስጠት እንደታሰበ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጋበዙት ሲ/ር ገነት ሀብታሙ እራሳቸውን ሲያስተዋውቁ በነርሲንግ እያገለገሉ እንደሚገኙና ሁለተኛ ድግሪያቸውን በስነ- ምግብ (Nutrition) መያዛቸውን ለማህበሩ አዲስ አባላት ካስተዋወቁ በኋላ በ Gynecology and Obstetrics በኩል የሚድዋይፈሪ ባለሙያዎችም መኖራቸውንና የሚያስፈልጋቸውን ግብአቶች ይዘው መምጣታቸውን ገልፀዋል፡፡
በመቀጠል ከሀገረ አሜሪካ የመጡትን ሲ/ር ቤተልሔም ጌጡ ራሳቸውን እንዲህ በማለት አስተዋውቀዋል። “ሲ/ር ቤተልሔም የአይ. ሲ.ዩ ነርስ (ICU nurse) ባለሙያ ስሆን እስከዛሬ ድረስ ማህበሩ እያከናወነ ያለውን መልካም ተግባር በቅርብ እርቀት ላይ ሆኜ እየተከታተልኩና ከማኅበሩ የቦርድ አባላት ጋር ብዙ ጊዜ መወያየት የቻልኩ ሲሆን ዛሬ በአካል አፋር የሚገኙ ወገኖቻችንን ለመርዳት በሚደረገው ዘመቻ ላይ በአካል በመገኘቴ የተሰማኝን ላቅ ያለ ደስታ ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡ ማኅበሩን ከውጭ ሆነው በብዙ ነገር እየደገፉ ያሉትን ወንድምና እህቶች እንዲሁም በሀገር ውስጥ ያላችሁ ባለ ቅን ልብ የሕክምና ባሙያዎችን ለማመስገን እወዳለሁ፡፡ የዛሬውን ጉዟችን የሰመረ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ።” ሲሉ መልካም ምኞታቸውን አጋርተዋል።
ከዚህ በመቀጠልም የማኅበሩ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ዘላለም ይርጋ የአሁኑ የህክምና ጉዞ ከወትሮ በተለየ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ህጻናት አልሚ ማግብ መያዙንና አገልግሎቱንም ለመስጠት ሁለት ቀናት ማደር እንደሚስፈልግ ገልጸዋል። ለዚህ የህክምና ዘመቻ የሚያስፈልጉትን ወጪዎች እኔም ለሀገሬ በሃምፕተን ሮድስ ቨርጂኒያ የኢትዮጵያውያን መረዳጃ ማህበር በተገኘ ድጋፍ የሸፈነ በመሆኑ ከልብ በማኅበሩ አባላትና ድጋፍ በሚያስፈልገው የአፋር ህዝብ ስም አመስግነዋል፡፡
በመጨረሻም ዶ/ር ዘላለም ተጨማሪ ሀሳብ መስጠት ለሚፈልጉ አባላት እድል እንደሚሰጡ በገለጹት መሰረት ሲ/ር አማነሽ ትዕዛዙ የአይ ሲ ዩ ነርስ ባለሙያ እንደሆኑ ገልጸው ፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገኙ ተረጂዎችን ለመርዳት የአይሲዩ ባለሙያዎች በመካከላችን በመገኘታቸውና የተሳካ አገልግሎት አከናውነን እንደምንመለስ ያላቸውን እምነት አስተላልፈዋል፡፡
ሹፌራችን በዉይይት ላይ መሆናችንን ተገንዝበዉ አቋርጠዉት የነበረዉን መዝሙር በመክፈት ልባችንን መዝሙሩ ላይ አይናችንን የገጠሩ የህብረተሰብ ክፍል አኗኗር ላይ አድርገን እንዲሁም የኑሮ ሁኔታቸዉን በግርድፉ ከአዲስ አበባ ነዋሪ ጋር እያወዳደርን መተሐራ ላይ ከረፋዱ 4፡05 ደቂቃ ደረስን። እለቱም ቀዳሚ ሰንበት (ቅዳሜ) በመሆኑ ለቁርስ ወርደን ተመግበን ከጨረስን በኋላ 4፡45 ላይ መተሐራን ለቀን ጉዟችንን በመቀጠል ወደ ዱፍቲ ሆስፒታልና ጭፍራ መጠለያ ጣቢያ አቀናን።
በአዉራ ጎዳና ግራና ቀኝ ላይ የምናገኛቸዉ እጽዋት ‹‹የፀሀዩ ንዳድ ያጠቃት በብዙ ጠዉልጎ የሚታይ የቅጠሏ ወዙ………›› ብለዉ የገጠሙት ክብር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል በአፋር መንገድ ላይ ሆነዉ መሆን አለበት ያስብላል፡፡
የአምላክ ፈቃድ ሆኖ ፀሎታችንንም ሰምቶ ያለ አንዳች እንቅፋት 9፡30 ላይ በተዘጋጀልን ናዝሬት ሆቴል ቅጥር ግቢ ውስጥ ገባን። የሆቴሉ አስተናጋጆች ብርሃን ፈገግታቸውን ሲያሳዩን ምንም እንኳን የመንገዱ ርቀት ያኽል ድካም ባይሰማንም ከአራት ሰዓት በላይ በመቀመጣችን ምክንያት የተፈጠረብንን የድካም ስሜት አባረው አንዳች መነቃቃት እንዲፈጠርብን ማድረግ ችለዋል፡፡ ተጨንቀውና ተጠበው ያዘጋጁልንን ምግብ በልተንና ጠጥተን ሆቴል ሳይሆን የዘመድ ድግስ ቤት የታደምን ያልመሰለው አንድም ሰው ማግኘት አይቻልም፡፡ ብሉልኝ ጠጡልኝ ተብለን የአፋርን ህዝብ እንግዳ ተቀባይነትና መልካምነት ገና በማለዳው ስራ ሳንጀምር ተረድተናል፡
ዶ/ር ዘላለም ይርጋ በሰላም ያደረሰንን አምላክ አመስግነው ለነገ ስራችን መቃናት የዱብቲ ሆስፒታልን መጎብኘት እና በተለይ ቀዶጥገና እና የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት የሚያስፈልጋቸውን ተረጂዎች ለመለየት ይረዳን ዘንድ ወደ ዱብቲ ሆስፒታል አቀናን። የሆስፒታሉን ኃላፊዎች በማግኘት ስለመጣንበት ዓላማ ገለጻ አደረግን። የሆስፒታሉም ኃላፊዎች መምጣታችን በእጅጉ እንደሚጠቅማቸው በአጽንዖት ገልጸውልናል። ከመካከላችን የኦ አር ቲም (OR team) ስራውን በቀጥታ መጀመር ያስፈልገውም ስለነበር እስከ ምሽቱ 1፡30 ድረስ በሆስፒታሉ ያሉትን የፕላስቲክ ሰርጀሪ ፣ፒኦፒ ፣ ካስት እና የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት (plastic, surgery, POP, and physiotherapy) የሚያስፈልጋቸውን የሆስፒታሉ ተረጂ ታካሚዎች በመለየት ለቀጣዩ ቀን እንዲዘጋጁ ከተደረገ በኋላ ለእራት ወደ ሆቴላችን ተመልሰናል። ጭፍራ ያሉትን ወገኞቻችንን ለመርዳት የግድ ከንጋቱ 11 ፡00 ሰዓት መነሳት እንዳለብን ተነጋግረን ለሆስፒታሉ አገልግሎት የሚሆኑትን መድኃኒቶችንና መሳሪያዎችን ኦ. አር ቲም (OR team) በሚገኝበት ሆቴል አሳደርን።
እንዲሁም ለተፈናቃዮች የሚሆኑትን መድኃኒቶች ከተለዩ በኋላ አምስቱ የማህበሩ አባላት እስከ ምሽቱ 5፡30 ድረስ የመጡትን መድኃኒቶች በቀጣዩ ቀን በየምድባቸው ለማድረግ በቂ ግዜ ስለማይኖረን በዕለቱ ማሰናዳት ስለነበረብን የመድሓኒቶችን ብዛትና አይነት ለይተን ለማስፈር ተሞክሯል፡፡ ይህንንም የመድኃኒት ዝርዝር ለባለሙያዎች በየግል ስልካቸው መላክ በመቻሉ ለስራው መቃናት በጎ አስተዋፅዖ ማበርከቱን ማወቅ ችለናል።
በቀጠሯችን መሰረት ከንጋቱ 11፡00 ላይ በጭፍራ የተፈናቃዮች ጣቢያ አገልግሎት ለመስጠት የተመደቡ አባሎችን ይዛ መኪናችን በሚሌ በኩል ወደ ጭፍራ ያመራን ሲሆን፤ የመልክዓ ምድሩ ሁኔታ ቀልባችንን እየገዛው ከአፋር ወደ ባቲ በሚወስደው አውራ መንገድ ላይ ከዋናው ከተማ 70 ኪሎ ሜትር ከተጓዝን በኋላ በቦታው ላይ የሚገኙትን ወገኖቻችንን ስንመለከት አንዳች ውስጥን የሚረብሽ እንግዳ ስሜት ተሰምቶን ነበር።
ኢንስፔክተር ሀይደር ከመኪናው በመውረድ የአፋርን ልጆች በቋንቋቸው በማውራቱ የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ የሚለው አባባል እውነታነቱ ከፍ ያለ እንደሆነ ተረድተናል። የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ከታካሚው ጋር መግባባት በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነው። ይህንንም ኢንስፔክተር እና በቦታው ላይ ያሉ የጤና ባለሙያዎች በቋንቋ ምክንያት ሊፈጠር የሚችለውን ክፍተት ስለቀረፉልን ቀልጣፋ አገልግሎት እንድንሰጥ ረድቶናል፡፡
ኢንስፔክተር ሀይደር በቦታው ላይ ያሉትን ኃላፊዎች ካነጋገረልን በኋላ መልካም ፈቃዳቸው ሆኖ በቀጥታ ቦታውን በማስተካከል ከጠዋቱ 3፡30 ጀምሮ አገልግሎት መስጠት ተጀምሯል። በዋናነት አገልግሎቱ ያካትት የነበረው የውስጥ ደዌ፣ የህጻናት፣ የማህጸንና ጽንስ፣ የስነ አእምሮ እና የአይን ህክምናዎች ይገኙበታል፡፡
የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ካርድ ይሰጣቸውና ልየታ ላይ ቫይታል ሳይን (vital sign) ከተወሰደ በኋላ ወደሚመለከተው ክፍል በመሄድ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን ችለዋል፡፡ በተለያየ ምክንያት ከመጠለያ ድንኳናቸው ወጥተው ወደ ተዘጋጀው ስፍራ መምጣት የማይችሉ ይኖራሉ ተብሎ ስለታሰበ ሶስት ባለሙያዎች የቤት ለቤት ስራውን በተሳካ ሁኔታ ሊያከናውኑልን ችለዋል። እንደተለመደው የልየታውን ስራ በግንባር ቀደምትነት የምግባረ ሰናይ ሆስፒታል ሰራተኞች አከናውነውልናል፡፡ አገልግሎቱን በምንሰጥበት ወቅት የካርድ እጥረት ቢያጋጥመን እንኳን ወረቀቶችን በማዘጋጀት ስራችንን እስከ 7፡30 ድረስ ለመቀጠል ችለናል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የሚድዋይፈሪ እና የስነ አእምሮ ባለሙያዎች ቤት ለቤት ባደረጉት የሕክምና ድጋፍ ፖስት ትራውማቲክ እስትረስ ዲስ ኦርደር (post-traumatic stress disorder or PTSD) በከፍተኛ ሁኔታ እንዳጋጠማቸው መረዳት ተችሏል። ብዙዎች በ PTSD, depression እና ጭንቀት ተጠቂ ሲሆኑ ወጣቶችና ህጻናትም ከትምህርት ገበታቸው በመስተጓጎላቸው እንዲሁም ሞት፣ ጥፋትና ውድመትን በመመልከታቸው እና አንዳንዶቹም ከወላጆቻቸው በመለያየታቸው ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ይታይባቸው ነበር። የዘርፉ ባለሙያዎችም ያላቸውን ክህሎትና እውቀት ተጠቅመው በግልና በጋራ የምክር አገልግሎት ለመስጠት ተችሏል። በመጨረሻም ከአገልግሎት የተረፉንን መድኃኒቶች ለጤና ባለሙያዎች አስረክበናል።
በጭፍራ የመጠለያ ጣቢያ በተካሄደው የህክምና ዘመቻ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑ ተፈናቃዮች ብዛት: –
- በውስጥ ደዌ (Internal Medicine): 185
- በህጻናት (Pediatrics): 169
- በማህጸንና ፅንስ (Gynecology and Obstetrics): 62
- በዓይን (Ophthalmology): 41
- Nutrition: 960 ካርቶን አልሚ ምግብ በምግብ እጥረት ተጠቂ ለሆኑ ህጻናት፣ እናቶች እና 32 የ HIV ህሙማን ታድሏል።
- በስነ አእምሮ ሕክምና፡ 110 ታካሚዎች ሲረዱ፤ ከነዚህም ውስጥ
- ከ 23-86 ዓመት እድሜ የሚገኙ 36 ሴቶች
- ከ 7-11 ዓመት እድሜ የሚገኙ 48 ልጆች
- ከ 14-18 ዓመት እድሜ የሚገኙ 26 ወጣቶች አገልግሎት ለመስጠት ተችሏል።
በጠቅላላው 527 ወገኖቻችን በጭፍራ የመጠለያ ጣቢያ አገልግሎት ማግኘት የቻሉ ሲሆን የተወሰኑት ከአንድ በላይ አከግሎት ተጠቃሚ ነበሩ። 6 ታካሚዎችም ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ዱፍቲ ሆስፒታል በሪፈራል ተልከዋል።
በዱብቲ ሆስፒታል ደግሞ በተካሄደው ህክምና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑ የታካሚዎች ብዛት
- ፕላስቲክ ሰርጀሪ (plastic surgery) ፡ 4
- ፊዚዮቴራፒና ካስት (Physiotherapy and applying cast with POP) ፡ 52
በድምሩ 56 ታካሚዎች በዱብቲ ሆስፒታል የቀዶጥገና፣ የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት እና የካስት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።በአጠቃላይ በዱብቲ ሆስፒታልና በጭፍራ የመጠለያ ጣቢያ በተካሄደው የሕክምና ተልዕኮ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ብዛት 583 ናቸው፡፡
በመጨረሻም በሁለቱም ቦታዎች የነበሩት ባለሙያዎች ሀሳብና አስተያየት እንዲሰጡ ከተደረገ በኋላ ወደ መኝታችን በማምራት ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት ላይ ለአፋር ሕዝብ ሰላሙ እንዲመለስለት በመመኘት አፋርን ተሰናብተን ፤ ወደ አዲስ አበባ በሰላም ተመልሰናል፡፡
በአፋር ላደረግነው የሕክምና ተልዕኮና ጉዞ መሳካት የረዱንን በሙሉ ለማመስገን እንወዳለን በተለይም ይህን አገልግሎት በገንዘብ ለረዱን “እኔም ለሀገሬ በሀምፕተን ሮድስ ቨርጂኒያ የኢትዮጵያውያን መረዳጃ ማኅበር” የላቀ ምስጋና እናቀርባለን። በመቀጠልም የአፋር ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰኢድ፣ የዱፍቲ ሆስፒታል ዳይሬክተር መሐመድ የሱፍ፣ የአፋር ማገገሚያ ጣቢያ ኃላፊ ሼክ ኑሪ፣ የጭፍራ መጠለያ ጣቢያ ኃላፊ አቶ መሐመድ፣ አቶ ኢብራሒም አለሙ በሎጂስቲክስ አገልግሎት፣ ኢንስፔክተር ሀይደር የፌዴራል ፖሊስ ሆስፒታል ሰራተኛ፣ ናዝሬት ሆቴል በምግብ አቅርቦት፣ ቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል በመረጃ አቅርቦት፣ የአለርት ሆስፒታል ሙሉ የ OR team ከአስፈላጊ ግብዓቶች ጋር ስለ ረዱን እና በመጨረሻም በዚህ ተልዕኮ የተሳተፉ የማኅበራችን አባላትና የጤና ባለሙያዎች በሙሉ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ በሆኑ ወገኖቻችን እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር ስም ምስጋናችንን እናቀርባለን።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማኅበር ለሁሉም በሁሉም!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!
ጥር 1/2014 ዓ.ም